
የብሪታንያዋ የጤና ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል!
የብሪታንያዋ የጤና ሚኒስትር ናዲን ዶሪስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ። የወግ አጥባቂው የፓርላማ አባል የሆኑት ሚኒስትሯ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፥ አሁን ላይ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እንዲቆዩ ተደርጓል ነው የተባለው።
ዶሪስ በቫይረሱ የተጠቁ የመጀመሪያዋ የፓርላማ አባል ሲሆኑ፥ አሁን ላይ በሃገሪቱ 382 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ ስድስት ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል። የ62 አመቷ ሚኒስትር ላይ ምልክቱ ካለፈው ሳምንት ሃሙስ ጀምሮ ሳይታይባቸው እንዳልቀረም ተገልጿል።
ይሁን እንጅ በእነዚህ ቀናቶች በተካሄዱ የካቢኔ ስብሰባዎች ላይ ከምን ያህል ሰዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አልተገኙም። ይህን ተከትሎም የሃገሪቱ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት ሚኒስትሮችና የፓርላማ አባላት ላይ ምርመራ ለማድረግ ስለማሰቡ ገልጿል።