ተጨማሪ መረጃ፦
ቢቢሲ የካቲት 25 እና 26/2012 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጉራጌ ዞን ኮኪር ገደባኖ ጉታዘር ወረዳ፤ መሃል አምባ ከተማ የሚገኝ የሙሉ ወንጌል አጥቢያ ላይ ጥቃት መድረሱን የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት የሆኑት መጋቢ ይልማ ሙሉጌታ መናገራቸውን ዘግቧል።
መጋቢ ይልማ ቤተክርስቲያኒቷ በአካባቢው ከ25 ዓመት በላይ የኖረች መሆኗን ጠቅሰው “በአካባቢው የሚገኙ የሐይማኖት አክራሪዎች ከምሽቱ 3፡30 ላይ አፍርሰዋታል” ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም በወቅቱ በቦታው ላይ የነበሩ ምዕመናን ላይም ድብደባ መፈፀሙንና ሰባት ምዕመናን መታሰራቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ ባሻገርም ቀደም የነበረው የአምልኮ ቦታ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉንና የነበረው ንብረት መውደሙን ተናግረዋል።
ታስረው ከነበሩት ሰባት ምዕመናን መካከል ስድስቱ ትናንት መፈታታቸውን የሚናገሩት መጋቢ ይልማ፣ አንዱ ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በከተማው የሚገኙ ከ40 በላይ የቤተክርስቲያኒቷ አባላት ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ጎረቤት ወደ ሆነው የኦሮሚያ ክልል በመሸሽ በሀርቡ ጩልሌ ሙሉ ወንጌል ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ምንጭ፦ BBC