
ፓስፖርት በ1 ወር ጊዜ ውስጥ መሰጠት ሊጀመር ነው!
የፌደራል ኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ፓስፖርት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መስጠት ሊጀምር መሆኑን ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል እንደገለጹት፥ ከዚህ ቀደም አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ሁለት ወር ከ15 ቀን በላይ ይወስድ የነበረው ጊዜ ወደ አንድ ወር ዝቅ እንዲል ተወስኗል።
በአዲሱ አሰራር መሰረት ፓስፖርት በአስቸኳይ ለማውጣት እስከ አምስት ቀን ብቻ እንደሚወስድም ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ በፓስፖርት ወረቀት እጥረት ምክንያት የአዲስ ፓስፖርት መስጫ ጊዜ ከአንድ ወር ወደ ሁለት ወር ከ15 ቀን መራዘሙ ይታወሳል።
በአሁኑ ሰዓት ኤጀንሲው ከ270 ሺህ እስከ 300 ሺህ ፓስፖርት እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይ 500 ሺህ ፓስፖርት ለማስገባት ስምምነት መደረሱን ገልፀዋል።