ተፅኖ ፈጣሪው ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ ከ 17 አመት በፊት ተማሪ እያለ በ ሲንጋፖር ካምቦዲያ የነበረውን ስርአት በዚ መልኩ ያስታውሳል 👇

የዛሬ አስራ ሰባት ዓመት አካባቢ ስኮላርሺፕ አግኝቼ መጀመሪያ ወደ ሲንጋፖር ነበር ያቀናኹት፡፡ በአንድ የግማሽ መንፈቀ-ዓመት እርፍት ወቅት ከሲንጋፖር አቅራቢያ የምትገኘውን ካምቦዲያ የምትባል ሀገር ልጎበኝ ሄድኹ። እኔ ወደዚያ ያቀናሁት የዕረፍት ጊዜዬን እነዚያ ስመ-ገናና የአንኮር መስህቦችን ለማየት ነበር። እግረ መንገዴን ግን ሀገሪቷ ያለፈችበትና እስከአሁንም ድረስ ሰቆቃው ያልደበዘዘውን ዘግናኝ የጭፍጨፋ ታሪክ ሰማኹ። ጭፍጨፋ የተካኼደባቸውንና ዜጎች በጅምላ የተቀበሩባቸውን ስፍራዎች በሕይወት በተረፉ ሰዎች ተራኪነት ጎበኘሁ። ታሪኩ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው … በ1975 እ.ኤ.አ ፖል ፖት በሚባል ሰው የሚመራው የኻሜር ሩዥ ቡድን በካምቦዲያ ሥልጣን ተቆጣጠረ። ቡድኑ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከምሁራን፣ መምህራን፣ ተቃዋሚዎች ወዘተ የሚቀርብበት ትችት ላሰበው ‹‹አብዮት›› ጸር እንደኾነ ተገነዘበ። ይህን ትችት ለምቋቋም እና ሥልጣኑን ለማጠናከርም የተማረውን ክፍል ከማጣጣል አልፎ የሀገሪቱ ችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርጎ መፈረጀ ጀመረ። ምሁሩን እንደ ጸረ አብዮት፣ ችግርን መተንተን እንጂ መፍትሄ መሻት የማይችል፣ መንግሥትን ከመተቸት አልፎ ማገዝ የማይፈልግ የሰነፍ ቅምጥል፣ የውጪ ኋይል ተላላኪ፣ ከተፈጥሮ ጋር ታግሎ የሚኖረው ገበሬ ተለጣፊ ወዘተ በማለት በመንግሥት ሚዲያ ዘመቱበት፡፡ ካድሬውም የስም-ማጥፋት ዘመቻውን አጧጧፈው። ይባስ ብሎ የኻሜር ሩዥ ቡድን አባላት ልሂቃኑ ካልተወገዱ ‹‹አብዮቱ›› ግቡን አይመታም ወደሚል መደምደሚያ ተሸጋገሩ።
በውሳኔው መሠረት ሕዝቡን ከምሁሩ ተጽዕኖ የማጽዳት ዘመቻ ተጀመረ። መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ reeducation camp (እንደ እኛ ሀገሮቹ ጦላይ፣ ብር-ሸለቆ ካምፖች ማለት ነው) ተወስደው ተረሸኑ። እድለኛ የኾኑት ገበሬ ኾነው የእርሻ መሬት እንዲያርሱ ተደረገ። ዩኒቨርሲቲዎች የቆሻሻ ሐሳብ ማፍለቂያ ተብለው ( litertally) ወደ እንሰሳት ማርቢያና በረት ተቀየሩ። የማጽዳት ዘመቻው በምሁራን ብቻ አላበቃም።
የከተማው ሕዝብ በምሁራኑ ጸረ-አብዮት አመላካከት እና የኑሮ ዘይቤ ተበክሏል ስለተባላ ከተሞችን ባዶ ያደረገ የማፈናቀል ዘመቻ ተካኼደ። ከጅምላ ርሸናው የተረፈው ከተሜ ወደ ገጠር በገፍ ተግዞ የእርሻ ‹‹አብዮት›› እንዲያካሂድ ግዳጅ ተጣለበት፡፡ የምሁራኑ መወገድና የከተሞች መራቆት ኢኮኖሚውን በእንፉቅቅ አስኬደው። ረሃብ ሰተት ብሎ ለመግባት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ከጥይት ርሸና የተረፈው በረሃብ አለቀ። በዚህ መልኩ የኻሜር ሩዥ አምባገነናዊ ቡድን በሥልጣን በቆየበት 4 አጭር ዓመታት (1975-1979) እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጋ (የሀገሪቱን 25%) ሕዝብ ለሞት ዳረገ።
የጠ/ሚነስትር ዐብይ አሕመድ የትናንት ምሁራዊትን የሚያጣጥልና ለማሸማቀቅ ረዥም ርቀት የተጓዘው ንግግር በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ በደብዛዛው ሲታይ የነበረውን ጸረ-ምሁራዊነት አዝማሚያ ገሀድ ያወጣ ክስተት ኾኖ ተመዘግቦ አልፏል፡፡ ጸረ-ምሁርነት (anti-intellectuali
sm) ማለትም ፖሊቲከኞች የሚያራምዱት የልሂቃንና ምሁራን ጥላቻ እና ፍራቻ የሀገርን ዓይን አጥፍቶ የሚያሳውር አደገኛ አመለካከት ነው። ምሁርነት እና ምሁራንን ማጣጣል ብሎም ማጥላላት በትንሹ ማኅበረሰቡ በተለይ ታዳጊ ሕጻናት እና ወጣቶች ለትምህርት እና እውቀት ያላቸው ክብር እና ምኞት እንዲቀንስ ያደርጋል። ባስ ሲል ደግሞ ከላይ እንዳየነው የምሁራን ፍጅት እና የሀገርን መድቀቅ ሊያስከትል ይችላል።
ካምቦዲያን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ ስፔን፣ አርጀንቲና አንዲሁም ጣሊያን ላይ ነግሰው የነበሩ አምባገኖች ጸረ-ምሁር ዘመቻ በማካሄድ ሺዎችን ገድለዋል። ጸረ-ምሁርነትን የሚሰብኩ ገዢዎች ብዙውን ጊዜ መዳረሻቸው ፋሺስታዊ አምባገንን መኾን ነው። ወደ ሀገራችን ስንመለስ ደርግ ምሁራኑ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ማስታወስ ይቻላል። የደርግ ቀይ-ሽብር ዘመቻ ተመሳሳይ አዝማሚያ የነበረውና ብሩህ አእምሮ የነበረውን አንድ የሀገራችንን ትውልድ የፈጀ ነው፡፡
ለኢሕአዴግም ጸረ-ምሁርነት አዲስ አይደለም። ትዝ ይለኛል የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ አንድ ያነበብኳት የኢሕዴግ/ኦሕዴድ ቢጫ መጽሐፍ ‘Hayyonni gurguddoon farra dimokraasiifi misoomati’ (ትላልቅ ምሁራን ጸረ ዲሞክራሲ እና ጸረ ልማት ናቸው) ትል እንደነበር አስታውሳለሁ። ባለፉት ሁለት ዓመታት የመንግሥት ባለሥልጣናት አካባቢ ስናየው የነበረው ምሁርነትን የማጣጣል ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ ዛሬ እዚህ ደረጃ ደርሷል፡፡ አሁን ደግሞ በግልጽ በሕዝባዊ መድረክና በቴሌቪዥን መቅረብ ጀምሯል።
በግሌ ይህ አካሄድ ሳይዘገይ እና ሳይከፋ ሊተች እና ሊታረም እንደሚገባው ይሰማኛል። እዚህ ላይ ምሁሩ አይተች ማለቴ አይደለም። ምሁሩ መተቸትና መነቀፍ አለበት። ምሁራኑ intelecual arrogance (ምሁራዊ እብሪት) እና elitism (እኛ ብቻ የተሻልን ነን) ዓይነት የአመለካከት ችግር ስላለባቸው በወጉ ሊነቀፉና ሊኼየሱ ይገባል፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ በተደጋጋሚ ምሁርነትን የሚያራክስና የሚያጥላላ ንግግር፤ በተለይ በሽግግር ወቅት ሲደረግ ውሎ አድሮ ወደ መንግሥት አቋምነት እያደገ ኼዶ መንግሥት እና ምሁራኑን ወደ ባላንጣነት የሚያሸጋግር መዘዙም ፋሺስታዊ አምባገነንነት እና የምሁራን ፍጅት ሊኾን ይችላል። ሳይቃጠል በቅጥል።

Published by Habesha Herald

We get you up to date News from every corner of the world .

Leave a comment

Design a site like this with WordPress.com
Get started