#በጣሊያን ሁለት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ መሞታቸው ታወቀ”የመጣውን (ሀዘን) ለመቻል ጥረት አደርጋለሁ። …በቻላችሁት ሁሉ ጥንቃቄ አድርጉ”💚💛❤

በጣሊያን ሁለት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ መሞታቸው ታወቀ
“የመጣውን (ሀዘን) ለመቻል ጥረት አደርጋለሁ። …በቻላችሁት ሁሉ ጥንቃቄ አድርጉ”

[የሟች ባለቤትና ቫይረሱ ይዟቸው ሻል ካላቸው በኅላ ከሆስፒታል የወጡ ኢትዮጵያዊ እናት በስልክ ከነገሩኝ የተወሰደ]

በጣሊያን ፓርማ ከተማ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ሁለት ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ማለፋ ታውቋል።
የዛሬ ሳምንት ማክሰኛ ዕለት ለአራት ቀናት ያህል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ያለፈው የ50 ዓመት ጎልማሳና የቢሮ ሰራተኛ የነበሩት ኢትዮጵያዊ አንዱ ናቸው።
እኚህ ኢትዮጵያዊ ባለትዳርና የሁለት ሴቶች አባት ሲሆኑ፣ ባለቤታቸውም በቫይረሱ ፖዘቲቭ ተብለው ለሁለት ቀናት ተኩል ያህል ቫይረሱን ለመከላከል በተዘጋጀው ልዩ ማቆያ የህክምና ክፍል ውስጥ፣ ህክምና ተከታትለው ወደቤታቸው በመሄድ ተጨማሪ ጥንቃቄና የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ በህክምና ባለሞያዎች ተመክረው መመለሳቸውን፣ ከሰዓታት በፊት የደረሰባቸውን ሁነት በከባድ ሀዘን ውስጥ ሆነው በስልክ አስረድተውኛል።
የጉንፋን ምልክቱ፣ ምግብ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ድካም ትከሳት፣ ተደጋጋሚ ደረቅ ሳል፣ ….ወዘተ ለሰባትና ስምንት ቀናት ከባለቤታቸው ጋር ካጋጠማቸው በኅላ ወደሆስፒታል እንደሄዱ የገለጹልኝ እኚሁ በሀዘን ተጉጂ ኢትዮጵያዊ ወ/ሮ፣ ባለቤታቸው ህመም ጠንቶባቸው የጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል (ICU) ውስጥ ገብተው በህክምና ቢረዱም በህይወት መትረፍ አለመቻላቸውን በእዝነት ነገረውኛል፣ የትዳር አጋራቸው የመተንፈሻ አካል ህመም (አስም) እንደነረባቸውም ይጠቅሳሉ።
ከባለቤታቸው ጋር ህይወታቸው ከማለፋ በፊት፣ አንደኛ ፎቅ እና ምድር ቤት ሆነው በስልክ ይነጋገሩ እንደነበረ በማስታወስም፣ እኔ ትንሽ ሻል ብሎኝ ከሆስፒታሉ ስወጣ ሃኪሞች ባለቤቴ ማረፋን ነግረውኛል ይላሉ። ሃኪሞች የቻሉትን ያህል እርዳታ እንደሚያደርጉ፣ የሰውን ህይወት ለማትረፍ ራሳቸውን መስዋዕት እስከ ማድረግ መድረሳቸውንም በበጎ ጎን ይጠቅሳሉ። ሆስፒታል የገባ ሁሉ አይሞትምም ባይ ናቸው።
ወደቤት ከተመለሱም በኅላ፣ የ18 እና የ16 ዓመት ሴት ልጆቻቸውም በቴክኖሎጂ መልዕክት ሳቢያ የአባታቸውን ማለፍ ማወቃቸውን አስረድተውኛል።
አያይዘውም፣ “አሁን ከቤት አንወጣም። ውጪውን በመስኮት ነው የምናየው። እኔም ሙሉ በሙሉ ነጻ ስባል ነው እኔም ልጆችም መውጣት የምንችለው። በቫይረሱ የሞተ ቤተሰብ ያላቸውና ታክመው ወደቤት የተመለሱ ሰዎች ክትትል ይደረግባቸዋል። ባለቤቴንም እስከአሁን አልቀበርነውም። በየዕለቱ ሰው ይሞታል። ቀብር ለሶስትና አራት ሰው ብቻ ነው የሚፈቀደው። የሚጠሩኝ ቀን እየጠበኩ እገኛለሁ። ማዘጋጃ ቤቱ ሟች በዝቶበታል። የሚሆነውን በሚዲያ እየተከታተልን ነው። ችግሩ ለሀገር፣ ለዓለም የመጣ ነው። የሀዘን ጨለማ ውስጥ ነው ያለነው። ያው የመጣውን ለመቻል ጥረት አደርጋለሁ ‘ ብለውኛል።
በማከልም፣ “ባለቤቴ የቢሮ ሰራተኛ ነው። በግል መኪና ነው ለስራ የሚመላለሰው። ከስራ ውጪ ብዙ ሰው የሚያገኝም አይደለም። ሱፐርማርኬት በመሄድ አስፈላጊ ነገሮችን ይገዛ ነበር። እኔ ግን በአውቶቡስ ነበር የምጠቀመው። በማን በኩል እንዴት ቫይረሱ እንደያዘን አናውቅም። አንዳንዴ፣ እኔ አውቶቡስ ስለምጠቀም አምጥቼበት ይሆን? ብዬ አስባለሁ። ግን እንዴት እንዴት እንደያዘን አላውቀውም። ህክምና ቦታ ሳንሄድ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታችንም የጎዳን ይመስለኛል። ሰዎች በቻሉት ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው” በማለትም ይመክራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ከኢትዮጵያ በቅርቡ ልጆቻቸው ጋር ጣሊያን የሄዱ አንድ ኢትዮጵያዊ እናትም ሰሞኑን እንደጉንፋን አድርጎ የጀመራቸው ህመም፣ የኮሮና ቫይረስ ሆኖ በመገኘት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስትያ ማረፋቸው ተሰምቷል።
በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው ያጡ ሰዎችንና ኢትዮጵያዊ ወገኖችን ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር። የሟች ቤተሰቦችንም መጽናናትን ይስጣቸው።

ኤሊያስ ገብሩ

Published by Habesha Herald

We get you up to date News from every corner of the world .

Leave a comment

Design a site like this with WordPress.com
Get started