ረጅሙ ፋኖን ማስፈራሪያ መግለጫ ከ አማራ ብልፅግና ፓርቲ

ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ!!


የተከበራችሁ የጎንደር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን፦
በአሁኑ ወቅት ከመሠረቱ እየተለወጠ ባለ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዓይነቱ አዲስ የሆነ ሪፎርም በማካሄድ ላይ ናት፡፡ ምክንያቱም የተለየ ታክቲክ ተከትለን ሪፎርም አካሂደን መለወጥ ካልቻልን ልማት ማስቀጠልም ማህበራዊ ሠላማችንን ማስጠበቅ አንችልም፡፡
ሀገራዊ ሆነ ክልላዊና አካባቢያዊ ለውጡ ሁለት መልክ ያለው ሲሆን እጅግ የሚያማልል ተስፋን የጫረ በተቃራኒውም ከፊት ለፊታችን ፈተናችንን የሚያበዙ ተግዳሮቶችም አሉብን፡፡
ስለሆነም በሀገራችን፣ በክልላችን ብሎም በከተማችን ከቀውስ የሚያወጣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድሎቻችን የሚያሰፋ የሪፎርም ታክቲክና ስትራቴጅ ተነድፎ እየተተገበረ ነው፡፡
የከተማችንን ሁኔታ ስንመለከት ሀገራዊ ለውጡ ጥሎን እንዳይሄድ ወደ ኋላ ከተጎተትን ሌሎቹ ከደረሱበት መድረስ ስለሚያቅተን በድሮ ስም፣ ክብርና ዝና ብቻ የዘመኑን ፈተና ማለፍ ስለማንችል ለሀገርም ለአለምም አስደማሚ የሆነ ከድሮ አባቶቻችን ክብርና ዝናችንን የሚመጥን ሁለንተናዊ ሪፎርም ውስጥ መግባት ግድ ይለናል፡፡
የጎንደር ከተማ ሁኔታ ከሀገራዊ ሁኔታ የሚያመሳስላት በአንፃሩም ደግሞ የተለየ የሚያደርጋት ሁኔታዎች አሉ፡፡
የከተማችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መድከም፣ የደህንነት ቀውስና አለመረጋጋት እንዲሁም የሠላም መታጣት በከተማችን ያለ ያለፋት ወደ 400 የሚጠጉ ዓመታት ያካበትነው የከተማነት ታሪካችን በእጃችን ያለውን የከተማችን ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቻችን እያሳጣን ነው፡፡
በከተማችን የፀጥታ የሠላምና የደህንነት ችግሮች የከተማው ህዝቦች አንድነት አለመጠናከር እዚያው ሳለ የከተማዋን ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና የንግድ እንቅስቃሴ ክፋኛ በመጉዳቱ የዚህን ችግር ምክንያት ማወቅ፣ መተንተንና ከመላው የከተማችን መፃኢ እድል እያሳሰባቸው ካለ ወገኖች ጋር መቅርቡ መለየት፣ መግባባትና ለመፍትሄው መሯሯጥ የግድ የሚልበት ምክንያት ዋነኛ የወጣቱ የሥራ እድል መፍጠሪያ እና የኢኮኖሚ ምንጭ ወደ መንጠፍ አቅጣጫ እየሄዱ በመሆኑ ነው፡፡
ከምንም በላይ የከተማችን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ኢ-ተገማች በመሆኑና ያልተረጋጋ በመሆኑ መዋከቡ ሲበዛና የከተማ አስተዳደሩ አመራርና ህዝብ ባልሰከነ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ የከተማዋን የሰላም መታጣት ችግር የበለጠ እያወሳሰበው መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ህገ ወጥነትና የጎበዝ አለቅነት እየተበራከተ እንዲመጣ አድርጓል፡፡
በዚህም የከተማችን ቅስም እስከወዲያኛው እንዲሰበር ለሚፈልጉ ለከተማው ክፋ የሚያስቡ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ኃይሎች በሙሉ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርን መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
የጎንደር ህዝብ አብዛኛው ወጣትና ትኩስ ሀይል ነው፡፡ ይህ የህ/ሰብ ክፍል የሥራ አጥነትና የኢኮኖሚ ችግር አለበት፣ በርካታ የጤናና ማህበራዊ ችግር እንዲሁም የከተማው የሠላምና የደህንነት መታጣት ችግር ይህንን የህ/ሰብ ክፍል የበለጠ ተጎጅ እያደረገው ነው፡፡
ስለሆነም የጎንደር ከተማ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ቅድሚያ የከተማው ህግና ሥርዓት ሠላም የሰፈነበት በማድረጉ ሂደት መሪ ተዋናይ በመሆን ከተማዋ የኢንቨስትመንት የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል እንድትሆን መስራት አለበት፡፡
የተከበራችሁ የከተማችን ህዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን
የአማራ ህዝብ እየታየ ያለውን ሀገራዊ ክልላዊ ለውጥ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ታግሏል፣ ደም ገብሯል፡፡ የጎንደር ከተማ ህዝብም የመጀመሪያውን የለውጥ ችቦ በመለኮስ ግፍና በደል እንዲቆም፣ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን፣ የማንነትና ወሰን ጥያቄዎች እንዲመለሱ የለውጡ ፋና ወጊነቱን ያስመሰከረ ህዝብ ነው፡፡
ለለውጡም መላው ህዝባችን ፋኖ ተሰማራ በሚል አኩሪ ገድል ፈፅሟል፡፡ አፋኙ ኃይል ወደ አንድ ጥግ እንዲገፋ አድርጓል፡፡ የክልላችን የለውጥ ሠራዊት የሆነው በክልሉ በተለይም በከተማችን ያለው ህዝባዊው ፋኖ ከለውጡ በኋላ መላ ቀልቡንና አቅሙን ወደ ልማት በማዞር ፀረ ድህነት ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተጓዳኝም የመላው የለውጥ ሀዋሪያ የሆነው የአማራ ህዝብ የወል መጠሪያ የሆነውን ፋኖን በማንገብ በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ የአማር ክልል ህዝቦች ጥቅም የሚጎዳ አመለካከትና ተግባርን በሰለጠነ አግባብ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየታገለ ይገኛል፡፡ እውነተኛው የፋኖ ንቅናቄ የመላው አማራ ክልል ህዝቦች የለውጥ ንቅናቄ መጠሪያ ሁኖ ለለውጡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ማንም ደፍጥጦት የሚያልፍ ጉዳይ አይደለም፡፡
ነገር ግን አሁን በተለይም በከተማችን እየተፈፀመ ያለው ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ፋኖነት በህዝብ አእምሮ ውስጥ ያለ በዋናነት የአማራ ክልል ህዝቦች አስተሳሰብ (Sentiment) ነው፡፡ ፋኖነት ህዝባዊነት ነው፡፡ ፋኖነት ለህዝብ ፍትህ፣ ለሠላም፣ ለልማት፣ ለአንድነት በአጠቃላይ ለተገፋ ህዝብ መቆምና መወገን ነው፡፡ ፋኖነት ለተጎዱ ላልተጠቀሙ ባይተዋርነት ለሚሰማቸው አጋር መከታ መሆን ነው፡፡ ፋኖነት ዘር፣ ሃይማኖት፣ ብሄር፣ ቋንቋ አይገድበውም፡፡ ፋኖነት የአድዋ፣ የማይጨው፣ የካራማራ፣ የ2008ቱ የጎንደር ህዝባዊ ማዕበል መጠሪያ ስም ነው፡፡
ፋኖነት ለተወሰነ ቡድን የተሰጠ ማዕረግ ወይም ሹመት አይደለም፡፡ ፋኖነት የህዝብ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ህዝባዊ የማዕረግ ስም እንጅ በህዝብ ስም የሚምሉ እና የሚገዘቱ የጥቂት ህገወጥ ቡድኖች የግል ጥቅም ማካበቻ ወይም የኑሮ ዘይቤ አይደለም፡፡
ነገር ግን አሁን በከተማችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአካባቢያችን ከትክክለኛው ፋኖ አላማ ውጭ በህገወጥ መንገድ የተደራጁ የታጠቁ ኃይሎች የተደራጁበት የውሸት ምክንያት የተለየ ከመሆኑም በላይ ጥቅም ማግበስበስ ዓላማ አድርጎ የተሰበሰበ ኃይል ነው፡፡
በዚህ ህገወጥ ቡድን መደራጀት በአሁኑ ወቅት ለህዝብ መታገል ሳይሆን የኑሮ ዘይቤ የመተዳደሪያ ገቢ ማግኛ ዘዴ ሁኗል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ለትክክለኛ ህዝባዊ አላማ ለመታገል መስሏቸው ተደራጅተው የህገወጡ ቡድን አጠቃላይ አካሄድ የሚፈፅማቸው ፀያፍ ድርጊቶች አልጥማቸው ሲል ራሳቸውን ያገለሉ አካላትን አብነት አድርጎ ማንሳት ይቻላል፡፡
በከተማችን ያለው ከዋናው ፋኖ አላማ ውጭ በህገወጥ መንገድ በቡድን ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን በርካታ ህገ ወጥ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለዚህም በቂ የሰው፣ የሰነድ፣ የኦዲዮ እና የቪዲዮ መረጃዎች አሉ፡፡ ከሚፈፅማቸው ህገ ወጥ ተግባራት መካከል ታጥቆና ተደራጅቶ በከተማው ይንቀሳቀሳል፣ ያለምንም ከልካይ ኬላ ጥሶ ከከተማ ይወጣል፣ ይገባል፣ ሰው ያግታል፣ ግድያ ይፈፅማል፣ ዘር ቆጥሮ የግለሰብ ቤት ነጥቆ ካምኘ ያደርጋል፣ ከባለሀብት በግዴታ ገንዘብ ይሰበስባል አንዳንዴም ይቀጣል፣ የከተማ መሬት ታጥቆ አጥሮ በመያዝ ቤት ይሰራል፣ በፖሊስ እጅ ያለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ እስር ቤት ጥሶ ገብቶ ያስፈታል፣ ህግ ጥሶ የወረደን የጦር መሣሪያ ታጥቆ ፖሊስ ጣቢያ በመውረር ዘርፎ ያመጣል፣ አስከሬን አጅቦ በመምጣት ጎንደርን በቶክስ ይንጣል፣ መሸታ ቤት ገብቶ ጠጥቶ አልከፍልም ይላል፣ በተደጋጋሚ በልዩ ልዩ የከተማው አካባቢወች ጥይት ይተኩሳል፣ ታዋቂ ግለሰቦችን በቡድን ተደራጅቶ የቡድን መሳሪያ ጭምር ታጥቆ ያጅባል፣ ታጥቆና ተደራጅቶ የመንግስት ተቋማትን፣ ፖርቲ ቢሮዎችን ይከባል፣ ያስፈራራል፣ አመራር ለመግደል እቅዶችን ያቅዳል፡፡
ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን እያወቀ የክልሉ መንግስትና የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ኃይል በሰለጠነና በሠላማዊ መንገድ ያለ ደም መፋሰስ ከዚህ ህገ ወጥ ድርጊቱ ታቅቦ የመንግስት ተገዳዳሪ ኃይል ሳይሆን ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት አድርጓል፡፡
በተለይም የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መስፈርቱን የሚያሟሉ ወደ ክልሉ የፀጥታ መዋቅር እንዲካተቱ፣ መተዳደሪያ የሌላቸው በከተማ ብድርና መስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲያገኙ፣ በኢንቨስትመንት አካባቢዎች በእርሻ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ደግሞ የእርሻ መሬት እንዲሰጣቸው፣ በቂ መተዳደሪያ ያላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በእነዚህ መፍትሄወች የማይስማማ ብቻ ለከተማችን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል መንግስት ህግን ለማስከበር እንደሚገደድ መፍትሄዎች አስቀምጧል፡፡
በእነዚህ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ከቀናት በኋላ ከክልሉ ከፍተኛ አመራር ጋር ውይይት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ በነበርንበት ጊዜ ሁሌም በህገወጥ መንገድ መቀጠል የሚፈልጉ የቡድኑ አባላት አዳዲስ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ፈፀሙ፡፡
እነዚህን የመፍትሄ አማራጮች እያሳየንና ብዙወቹ ፈቃደኝነታቸውን እያሳዪ ባሉበት ሁኔታ የህገወጡ ቡድን አባላት ጎንደር ከተማ ላይ ሀሙስ መጋቢት 10/07/2012 ከቀኑ 11 ሰአት ከአራዳ ክፍለ ከተማ ብጥብጥና ሁከት በማስነሳት ከጀርባው በአካባቢው ባሉ የህገወጡ ቡድን ታጣቂዎች ታጅቦ የመኪና መንገድ በልዩ ልዩ ቁሳቁሶች እየዘጋ ልዩ ልዩ ፅንፈኛ መፎክሮችን እያሰማ ወደ ዞኑ ፖሊስ መምሪያ በመሄድ በህንፃውና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተሞከረ ሲሆን አመፁንም የከተማችን የፀጥታ ሀይል በፍጥነት ደርሶ በትኖታል፡፡
ይህ ምልክት ማምሻውን ተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ ለማቀጣጠልና ከተማዋን ወደ አጠቃላይ ቀውስ ለመውሰድ የሚደረግ ዝግጅት መኖሩን ያረጋገጠው የከተማችንና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጋራ ኮማንድ ፖስት የህዝባችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ተጨማሪ የፀጥታ መዋቅር በተመረጡ አካባቢዎች ስምሪት አደረገ፡፡
በዚሁ እለት ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ማራኪ ክፍለ ከተማ ሽዋ ዳቦ አካባቢ በአካባቢው ሲያልፋ የነበሩ በአካባቢያችን የተሰማራ የመንግስት የፀጥታ ሀይል አባላት ላይ በተከፈተ ቶክስ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል፡፡
ይህ ታጥቆ ተደራጅቶ በፀጥታ ሀይላችን የህይወት መስዋትነት እየከፈለ በዚህ ህገወጥ ቡድን ተመሳሳይ አፀፋ መሰንዘር አልተፈለገም ነበር ይልቁንም የፀጣታ ሀይላችን የህዝብ ልጅ መሆኑንና ዳግም ህዝባዊነቱን ያስመሰከረበት አኩሪ ገድል ነበር፡፡
ይህንን ጉዳት ያደረሰው ህገወጡ ኃይል ይህንን ድርጊት ከፈፀመ በኋላ በህገወጥ መንገድ ወደመሸገባቸው ቦታወች ሸሽተው በመደበቃቸው የክልላችን የፀጥታ ሀይል አባላት የመሸገበትን አካባቢ በፍጥነት ለመቆጣጠርና ጥቃት አድራሹን ቡድን በቁጥጥር ሥራ ለማዋል ፈጥኖ ቦታዎችን ቢቆጣጠርም ቡድኑ ቶክስ ከፍቶ ከአካባቢው ተሰውሯል፡፡
የተከበራችሁ የከተማችን ህዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን
ችግሩ በዚህ ብቻ አላበቃም በሚቀጥሉት ቀናትም ህገ ወጥ ሰልፋ፣ ህገ ወጥ የስራ ማቆም አድማ ለማካሄድ ከመሀል አገር አዲስ አበባ ድረስ የተላኩ በተሽከርካሪ የታገዘ የአድማ ወረቀት የመበተንና በህገወጥ መንገድ የተደራጀው ህገ ወጥ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም አልያም ቡድኑ ጉልበቱ እንደፈረጠመ የፈለገውን ህገ ወጥ ስራ እየሰራ መንግስትን እየተገዳደረ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሌሎች ተላላኪ ኃይሎች በርካታ ጥረት አድርገዋል፡፡
ሁለቱም ድርጊቶች በሠላም ወዳዱ የጎንደር ህዝብና በፀጥታ መዋቅራችን የጋራ ጥረት አልተሳኩም፡፡ የጎንደር ህዝብ ልብ ሊል የሚገባው ጎንደር ቅስሟ እንዲሰበር በውስጥም በውጭም ያሉ ጠላቶቻችን ያለ የሌለ ሀይላቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡
የተከበራችሁ የከተማችን ህዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን
በህገወጥ መንገድ የተደራጀው ህገ ወጥ ቡድን ከመሸገበት አካባቢዎች እንዲለቅና እንዲበተን ከተደረገ በኋላ በዋናነት ሁለት ጎላ ጎላ ያሉ የህዝብ ስሜቶች በከተማችን ተፈጥረዋል፡፡
የመጀመሪያውና በርካታው የከተማችን ሆኑ በዙሪያው ያሉ ዞኖችና ወረዳዎች ህዝቦች በተወሠደው እርምጃ ከፍተኛ ደሰታ ተሠምቷቸዋል፡፡ ወደ ኃላ እንደትመለሱ ህግ አሰከብሩ፣ አጥፊን ጠይቁ ፣ከመንግሥት ጋር የሚገደደር ሀይል ይበተን፣ ሠላማችንና ደህንነታችንን መልሱልን ፣ የህዝባችን አንድነት አጠናክሩ፣ የሚል የጎሉ ሀሰቦች ተንፀባርቀዋል፡፡
በአንፃሩም ደግሞ ህገወጥ ቡድኑ እየፈፀመ ያለውን ድርጊት ትክክለኛ መረጃ ካለማግኘት በመነጨ መንግሥት የወሠደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ፋኖን ለማጥፋት ነው የሚል የተዛባ ትርክት አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ እየተሠማ ሲሆን መንግሥት የተደከመ ስለሆነ ዋስትናችንና የቁርጥ ቀናችን ይህ ቡድን ነው በሚል መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃውን ለማጣጣል ከተቻለም ለማደናቀፍ የሚጥሩ ጥቂት የውስጥና የውጭ ተላላኪ ሀይሎች ተስተውለዋል፡፡
አሁን በተጨባጭ ያለው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬውን እያረጋገጠ እየመጣ መሆኑ እየታወቀ እንደተባለው የአፈፃፀም ድክመት እንኳን ቢኖር በህግ በስርዓት የማይመራ ቡድን የፈለገውን እያደረገ ይቀጥል ከማለት የመንግሥት ድክመት ፈልጎ ተጋግዞ ማረም በተገባ ነበር ፡፡
መላው ሠላም ወዳዱ የክልላችን ሆነ የጎንደር ከተማ ህዝብ በተቃራኒው ደግሞ ጥቂቶቹ ለጎንደር ወድቀት ሌት ከቀን የሚጥሩ ሀይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ሀቅ ቢኖር በከተማው አስተዳደር እሰከለ ድረስ በህገወጥ መንገድ ታጥቆ ተደራጅቶ ከነፍስ ወከፍ እሰከ የቡድን መሳሪያ አንግቦና ካምኘ መስርቶ መኖር አይቻልም፡፡
የክልላችን መንግሥት ሆነ የከተማችን አስተዳደር የታጠቀን ህገወጥ ቡድን አይታገስም ፣ ህግ ያሰከብራል፡፡ የክልላችን ሆነ የከተማችን የውሰጥም ሆነ የውጭ የፀጥታ ችግር የሚፈታው በክልላችን እና በፌዴራል የፀጥታ ሀይሎች ብቻ እንጅ በሌላ በማንም ቡድን ሊሆን አይችልም፡፡
ስለሆነ የከተማችን ፀጥታ ችግር በባለቤትነት መፍታት ያለበት የከተማችን ህዝብና በተለይም ወጣቱ ከከተማችን ከክልላችንና ከፌደራል የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ነው ፡፡ ህዝባችን ሠላሙ የሚያረጋግጥለት ደግሞ የፀጥታ መዋቅራችን ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት እንጅ በሌላ በማንም ሀይል አይደለም፡የእስከአሁኑ ሂደታችንም በከተማችን ከሠላም ወዳዱ ህዝቦችን ጋር ተቀናጅቶ እየሠራው ያለው የፀጥታ መዋቅራችን የከተማችን የፀጥታ ሁኔታ በተለይም ዋና ዋና ወንጀሎች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀንስ አድርጓል፣ ቀጣይም በእልህና በወኔ ሰላም የማስከበር ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
የተከበራችሁ የከተማችን ህዝቦች በተለይም ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌወችና የሀይማኖት
ስለሆነም በቀጣይ የከተማ አስተዳዳራችን ከመላው የጎንደር ከተማ ሠላም ወዳድ ህዝብ ጋር በመሆን የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል፡፡ በከተማችን የተጀመረውን ህግ እና ስርዓት የማስከበር ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሠብ በከተማው ውሰጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ነው ፡፡
ይህንን የክልሉ መንግሠት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያ የጣሠ የያዘውን የጦር መሳሪያ አውርዶ በህግ የሚጠየቅ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
በማንኛውም ሁኔታ ህግ በጣሰ መንገድ የሚካሄድ የጥይት ቶክስ የያዘውን የጣር መሳሪያ አወርዶ በወንጀልና በፍትህብሔር እንዲጠየቅ ይደረጋል፡፡
በከተማችን ህገወጥ ሠልፍ፣ የተዳከመውን የከተማችን ኢኮኖሚ ጭራሽ ይበልጥ እንዲዳከም ህገወጥ የሥራ ማቆም አድማ ለማካሄድ የሚቀሰቅስ፣ የሚያነሳሳ ከዚህ ህገወጥ ድርጊቱ መቆጠብ ያለበት ሲሆን ተባባሪ የሆነ ሁሉም በህግ ይጠየቃል፡፡
በህገወጥ መንገድ የተደራጀው ነገር ግን አሁን የተበተነው ህገወጥ ቡድን በሠላም እጁን ለመንግስት እሰከ መጋቢት 20/2012 እንዲሠጥ ይህንን አልፈፅምም ካለ ቡድኑን የመንግስት የፀጥታ ሀይል ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን የምናረጋግጥ ሲሆን ለዚህም ህዝባችን ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
መላው የከተማችን ህዝቦች በተለይም ወጣቶች አሁን የተፈጠረውን አንፃራዊ ሠላም እና እድል ወደ ዘላቂ ሠላምና ልማት እንዲቀየር በማድረግ ጎንደር የሠላም፣ የፍቅር ፣የአንድነት ፣የኢንቨስትመንት፣ የቱሪስት፣ እና የንግድ ከተማ እንድትሆንና ወደ ቀደመ ክብሯና ገናና ታሪኳ እንድትመለስ አብረን ሌት ከቀን እንድንሠራ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
የከተማችን የክልላችንና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር የከተማችን ህዝብ ሠላሙ ዘላቂ እንደሆኑ እየከፈላችሁት ያለ መስዋትነት ታሪክ የማይዝነጋው መሆኑን አወቃችሁ አስተማማኝ ሠላም ሠፋኖ መላው የከተማችን ህዝብ በሙሉ ቀልቡ ወደ ልማት እስኪገባ ድረስ ሠላም የማስፈን ህግና ሥርዓት የማስከበር ህገወጥነትን የመከላከል ፣ አጥፊወችን ለህግ በማቅረብ ከሰላም ወዳዱ ህዝባችን ጋር በመሆን የህግ የበላይነትን እንድታረጋግጡ ጥሪያችን እናሳተላልፋለን ፡፡
በከተማችን ፣በክልላችን ሆነ በሀገራችን የምትገኙ ባለሀብቶች ሆናችሁ ዲያስፖራዎች ለከተማችን ልማት እያበረከታችሁ ያላችሁት አስተዋፅ እና ሁለንታዊ ድጋፍ ሁሌም እያደነቅን በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ገብታችሁ የከተማዋን ችግር በማወሳሰብ የተጠመዳችሁ ጥቂት የውጭና የውስጥ ሀይላት ለጎንደር ህዝብ ስትሉ ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የከተማችን የመንግሥት ሠራተኞች ፣መምህራን፣ የህክምና ባለሙያወች በሙሉ በየተሠማራችሀብት መስክ ህዝብ በፍፁም ታማኝነት፣ከመድሎ ከሙስና በፀዳ መንገድ የአገልጋይነት መንፈስ እንድታገለግሉት የህዝብ ጥያቄ እንድትመልሱ የአደራ መልዕክታችን እናስተላልፈለን ፡፡
ከዚህም ሌላ በከተማችን፣ በሀገራችን ሆኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምትገኙ የዲያስፖራ አባላት የማህበራዊ ሚዲያ እንቂወች /activist/ ብሎገሮችና የኮሚኒኬሸን ባለመያዎች ፣ነጋዴዎች፣አልሚ ባለሀብቶች ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር በመሆን በቅርቡ በከተማችን ለልማት ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን ስናበስራችሁ ለከተማችን የገፅታ ግንባታ እጅና ጓንት ሁነን እንድንሠራና ለጎንደር ትንሳኤ የበኩላችን አስተዋፅኦ እንድናበረክት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም መላው የከተማችን የሀይማኖት አባቶች እንደወትሯቹህ ከሀይማኖታዊ አስተምህሯቹሁና ከእምነት ተልኳችሁ አንፃር በተቃኘ አግባብ ሰላምን ልማትን አንድነትን ፍቅርንና መተሳሰብን እንድትሰብኩ የአደራ መልእክታችን እናደርሳለን፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት

Published by Habesha Herald

We get you up to date News from every corner of the world .

Leave a comment

Design a site like this with WordPress.com
Get started