ፕ/ር መረራ ያስነሱት አቧራና፣ ከፍተኛ አምባጓሮ የፈጠረው “የብሔራዊ ውይይት” ውሎ፣
(መሐመድ አሊ መሐመድ)
ነሀሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ በተዘጋጀው “የብሔራዊ ውይይት” መድረክ ላይ እኛም ታድመን ነበር፡፡ በዚህ መድረክ አጨቃጫቂ ጽሁፍ ያቀረቡትን ፕ/ር መረራ ጉዲናን በሻይ ሠዓት አግኝቻቸው ባቀረቡት ጽሁፍ እጅግ መደንገጤን ገልጨላቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ፕ/ር መረራ፣ በተለይ ለዶክትሬት (3ኛ ዲግሪ) መመረቂያቸው ” Ethiopia: competing ethnic nationalism and the quest for democracy, 1960-2000″ በሚል ርዕስ ባዘጋጁትና በመጽሐፍ መልክም ባሳተሙት የምርምር ሥራቸውና በሌሎችም ጽሁፎቻቸው አማካይ አቋሞችን በማራመድ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ፕ/ር መረራ ራሳቸው በዚህ መድረክ ባቀረቡት ጽሁፍ፣ “አሁን ለተፈጠሩት አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ ከማሳየት ባለፈ ሰፋ ባለ መልኩ ሚዛኑን የጠበቀ ነገር ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አልተሰጠኝም” በሚል የመድረኩን አዘጋጆች ይወቅሳሉ፡፡